የካቲት 26/2018 (ገበያ ሚዲያ) በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ዳርቻ በሚገኝ ሩዋይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ትናንት ረቡዕ በፖሊስ በተካሄደ ድንገተኛ ፍተሻ፤ በሕገ-ወጥ የሰዎች አጋቾች ታግተው የነበሩ 66 ኢትዮጵያውያን እና 4 ኤርትራውያን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የኬንያ መርማሪ ፖሊሶች አስታውቀዋል።
በድምሩ 70 የሚሆኑት እነዚህ ዜጎች የተገኙት በኬንያ የወንጀል ምርመራ መምሪያ ሥር የሚገኘው የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች መከላከል ክፍል ከሕዝብ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ባደረገው ኦፕሬሽን ነው ተብሏል።
ግለሰቦቹ በሩዋይ አካባቢ በሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው መገኘታቸውን የገለጹት መርማሪዎች፤ በወቅቱ አንድ ኬንያዊ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አረጋግጠዋል።
በዚህም የተረፉት ግለሰቦች ለፖሊስ በሰጡት ቃል በሀገራቸው ካለው ችግር በመሸሽ ለተሻለ ሥራ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ ማቀዳቸውን እና አብዛኛውን ጊዜ በሞያሌ ድንበር አቋርጠው ወደ ኬንያ እንደሚገቡ ከዚያም ወደ ደቡብ አፍሪካ ወይም መካከለኛው ምስራቅ እንደሚጓጓዙ መናገራቸው ተገልጿል።
ተጎጂዎቹ በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ጥበቃ ሥር የሚገኙ ሲሆን፤ ወደ ሀገራቸው ከመመለሳቸው ወይም ሌሎች ሕጋዊ ሂደቶች ከመከናወናቸው በፊት ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ተነግሯል።
በተጨማሪም ፖሊስ ዝውውሩን የሚያስተባብሩ የሕገ-ወጥ ቡድኖችን ሰንሰለት ለመበጠስ ክትትሉ ይቀጥላል ተብሏል።









