የካቲት 26/2018 (ገበያ ሚዲያ) በዛምቢያ ናኮንዴ ወረዳ የሚገኙ የጸጥታ አካላት፣ በነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ውስጥ ተደብቀው ወደ ሀገሪቱ የገቡ 21 ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያኑ የተገኙት ከታንዛኒያ ተነስተው ወደ ዛምቢያ በገቡ ሁለት የነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ውስጥ ተደብቀው ሲሆን፤ ተሽከርካሪዎቹ በናኮንዴ የድንበር ቀጠና ውስጥ በተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ በትናንትናው ዕለት መያዛቸው ተነግሯል።
ፍተሻው የተካሄደው በመድኃኒት ቁጥጥር ኮሚሽን፣ በዛምቢያ ፖሊስ እና በኢሚግሬሽን መምሪያ በጋራ በተደረገ ኦፕሬሽን መሆኑን ዛምቢያ ሞኒተር ዘግቧል።

ሁለቱም ቦቴዎች “ወርልድ ኦይል ሊሚትድ” ለተሰኘ ድርጅት የሚሰሩ ሲሆን፤ ከታንዛኒያ ዳሬሰላም ነዳጅ ጭነው ሲጓዙ እንደነበርም ነው የተገለጸው።
በቦቴዎቹ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ተደብቀው የተገኙት 21 ኢትዮጵያውያን ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 35 ዓመት ባለው ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ አብዛኞቹ በ20ዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ላይ ያሉ ወጣቶች ናቸው ተብሏል።
በተደረገው ምርመራም ወደደቡብ አፍሪካ ለመግባት የሚጓዙ መሆናቸው መታወቁ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የቦቴዎቹ አሽከርካሪዎች ፊሊበርት ፋውስቲን እና አሊኬጃ የተባሉ የታንዛኒያ ዜጎች ሲሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት በናኮንዴ ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን የሙቺንጋ ግዛት የፖሊስ ኮሚሽነር ዴኒስ ሙላ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ባለፈው እሁድ 15 ሌሎች ኢትዮጵያውያን በሕገ-ወጥ መንገድ ዛምቢያ ገብተው በአንድ ግንባታ ላይ ባለ ትምህርት ቤት ውስጥ ተደብቀው መገኘታቸው ተገልጿል።





